top of page
Image by Greg Rosenke

ወርኃ ጽጌ

   በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ ያለው ወቅት ወርኃ ጽጌ (የጽጌ/የአበባ ወር) ይባላል፡፡ በወርኃ ጽጌ አበባዎች ያብባሉ፤ ፍሬም ያፈራሉ፤   በዚህም ወቅት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ እንዲጠብቃት ከታዘዘው አረጋዊው ዮሴፍ ጋር ስትኖር መልኳ አንዳንድ ጊዜ እንደ ጽጌረዳ አበባ ቀይ ሁና፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እንደ ሮማን አበባ ነጭ ሁና ስትታየው፣  ቀይ የነበረው መልኳ ተለውጦ እንደ ሮማን አበባ ጸዓዳ ነጭ፣ ነጭ የነበረው እንደ ጽጌረዳ ቀይ ሲለወጥ በመደንገጥ እርሷ መሆኗን ለማረጋገጥ ‹‹ማርያም›› ብሎ እየጠራ ያረጋግጥ ነበር፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለዚህ ምሥጢር ሲያስረዳ ‹‹መልኳ እንደ ጽጌረዳና እንደ ሮማን አበባ ይለዋወጥበት ስለነበር በአንድ ዓይነት መልክ አላወቃትም›› ብሏል፡፡ በዚህም ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እመቤታችንን በአበባ፣ ጌታችንን ደግሞ በፍሬ እየመሰሉ ለማመስገንና ለማወደስ በሚያስችል ምሥጢር የስደቱ ጊዜ በወርኃ ጽጌ እንዲዘከር አድርገዋል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለዘለዓለሙ የማይደርቀውን የሕይወት ፍሬ ኢየሱስ ክርስቶስን ያስገኘችልን ንጽሕት የማትጠወልግ አበባ ናትና፡፡

 

    በነገረ ማርያምም እንደተጻፈው እመቤታችን መውለጇ ቀን ሲደርስ አረጋዊው ዮሴፍ ማረፊያ ቦታ ፈልጎ ከብዙ ድካም በኋላ ከብተቾች የሚያርፉበት በረት አግኝቶ እመቤታችንን በዚያ አሳረፋት፡፡  በከብቶች በረት ውስጥ ሳሉ እመቤታችን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወለደችው፤ በጨርቅ ጠቅልላ በበረት ውስጥ አስተኛችው፡፡

 

    ጌታችን ኢየሱስም ሁለት ዓመት ሲሞላው ኄሮድስ ሕፃኑ ክርስቶስን ሊገለው ስለፈለገ መልአኩ ‹‹ተነሥተህ እናቱንና ብላቴናውን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› ብሎ  ለዮሴፍ ነገረው፡፡ እመቤታችንም ከዮሴፍ ጋር ልጇን ይዛ ወደ ግብፅ ተሰደደች፡፡ (ማቴ.፪፥፲፫)

 

     ከአረመኔው ንጉሥ ኄሮዱስ ሽሽትም የተወደደ ልጇን ጌታችን ኢየሱስን ይዛ  በግብፅና በኢትዮጵያ ምድር ከአረጋዊው  ዮሴፍና ሰሎሜ ጋር ብዙ መከራና ችግር ደርሶባታል፡፡ በዚያን ጊዜ ሕፃን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ያድን የነበረው ንጉሡ ለዐራት ወታደሮቹ እና ጭፍሮቻቸው  እመቤታችንን ከነልጇ ይዘው ከመጡ የበለጠ ሹመትና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ነግሮ ላካቸው፡፡ የዮሴፍ ልጅ ዮሳ ይህንን ሲሰማ ለድንግል ማያርም ነገራት፤ እርሷም አምርራ አለቀሰች፡፡

 

    በግብፅ በርሃ ሲጓዙም እመቤታችን ወደ ትዕማን ቤት ሄዳ ነበር፡፡ የቤቱ እመቤት ባየቻት ጊዜ ‹‹ከየት መጣሽ? ብላ ጠየቀቻት፤ እመቤታችንም ‹‹ከይሁዳ ምድር የተሰደድኩ ስደተኛ ነኝ›› ብላ መለሰችላት፡፡ ‹‹አንቺ ሴት ደረቅ ነሽ መሰለኝ፤ በድርቅናሽ ቤትሽን ትተሽ ትዞርያለሽ፤ እንዳንቺ ያለች ቆንጆ ሴት ከአዳራሽ ወደ ዕልፍኝ ይላል እንጂ ሀገሩን ትቶ ሀገር ለሀገር አይንከራተትም›› ብላም ተተናኮለቻት፡፡ አረጋዊው ዮሴፍም ‹‹ለለማኝ ቢኖር ይሰጡታል፤ ባይኖር ደግሞ ካለበት ያድርስህ ይባላል እንጂ እንዲህ እንደ ፍላፃ ልብ የሚወጋ ነገር ምን ያናግርሻል›› ብሎ በተናገራት ጊዜ ኮቲባ የተባለችው የእመቤቲቱ ገረድ ‹‹ይህ ጀውጃዋ ሽማግሌ ደፍሮ እመቤቴን እንዲህ ይመልስላታል?›› ብላ ዮሴፍን በጥፊ ቃጥታ ሕፃኑን ደግሞ ነጥቃ ጣለችው፡፡ በዚያን ጊዜም ሕፃኑ ኢየሱስም አለቀስ፤ እመቤታችን እርሱን ተከተትላ ምርር ብላ አለቀሰች፤ ልታነሳውም በምትሞክርበት ጊዜ ዮሴፍ ‹‹ተይው፤ አምላክነቱ ይገለጽ›› ብሎ ከለከላት፡፡ ከመቅጽበት ሰዓት ትዕማንን ከገረድዋ ኮቲባ ጋር መሬት ተከፍቶ ዋጣቸው፡፡ ከዚህም በኋላ  ስድስት ወር ያህል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከልጇና ከዮሴፍ እንዲሁም ከሰሎሜ ጋር በዚያ ቤት ከተቀመጡ በኋላ እመቤታችን ልጇን እንዳይገሉባት በማሰብ ዱር ለዱር ተገልጿል፡፡ (ቅዳሴ ማርያም አንድምታ ትርጓሜ)

 

    በበረሃ እየተጓዙ ባለበት ሰዓትም ጥጦስና ዳክርስ የተባሉ ሁለት ወንበዴዎች አገኟቸው፡፡ የለበሱትን አልባሳት ገፈውም ወሰዱባቸው፤ ወንበዴዎቹም በመቀጠል ምን ማድረግ እንዳለባቸው ቊመው ሲማከሩ እመቤታችን ልጇን የሚገድሉባት መስሏት አለቀሰች፡፡ ሆኖም ግን ጥጦስ ካደረበት ፍቅርና ርኅራኄ የተነሣ ‹‹እነዚህ ሰዎች አሳዘኑኝ! ወደዚህ ቦታ የመጡት ያለ ምክንያት አይሆንምና አንቀማቸው እንተውላቸው›› ብሎ ልብሳቸውን መልሰላቸው፤ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉም ረዳቸው፡፡

 

    ከዚህም በመቀጠል እመቤታችን ሕፃኑ ልጇን ይዛ ወደ ኢትዮጵያ ተጓዘች፤ ኢትዮጵያውያንም  በፍቅር ሳስተው ተቀብለው አሳረፏቸው፤ እንዲያውም አንዳንዶቹም ቤታቸውን በመልቀቅ አስተናገዷቸዋል፡፡ ብዙዎችም ‹‹ደም ግባቱ ከሰው ልጆች ሁሉ ያምራል›› ተብሎ የተነገረለትን የጌታችንን መልክ በማየት ብቻ ለማመን በቅተዋል፡፡ አንዳንድ ሰይጣን ያደረባቸው ሰዎች ቢያጋጥሟቸውም በበረሃ ውስጥ የሚኖሩ ሽፍታዎችም ለጌታችን ያሳዩት ርኅራኄና ፍቅር የተለየ ነበር፡፡ እመቤታችን በኢትዮጵያውያን ደግነትና ፍቅር በመደሰቷ ጌታችን ኢትዮጵያን በእመቤታችን ምልጃ አስጠበቃት፤ የዐሥራት ሀገርም አድርጎ ሰጣት፡፡ ለፍቅሩ ሳስተው ለተቀብሏቸው ኢትዮጵያውንና ግብፃውያንም የግብፅንና የኢትዮጵያን ገዳማት ሲባርክ ሌሎችንም ገዳማት መሠረተላቸው፡፡ (ድርሳነ ዑራኤል)

 

     እመቤታችንም ከልጇ ጋር በግብፅ ለሦስት ዓመት ከስድስት ወር በስደት ኖራለች፤ ንጉሥ ኄሮድስም ከሞተ በኋላ የእግዚአብሔር መልአክ በሕልሙ ‹‹የሕፃኑን ነፍስ የሚሹት ሙተዋልና ተነሣ፤ ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ተመለስ›› አለው፡፡ አረጋዊው ዮሴፍም እመቤታችንንና ልጇ ኢየሱስን ይዞ ወደ እስራኤል ተመለሰ፡፡  (መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ግንቦት)

 

     እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በበረሃ መሰደዷን እያሰብንና በዓይኗ በፈሰሰው ዕንባ ብዛት ቸርነትና ምሕረትን እንድታሳስብልን የአምላካችን እግዚአብሔር ፍቃድ በመሆኑ ይህንን በማሰብ ወርኃ ጽጌን በጾምና በጸሎት እንማልዳለን፡፡ ጾሙ የፈቃድ ቢሆንም የእመቤታችንን ስደት ለማስታወስ እንጾማለን፡፡

ከጾሙ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን፡፡

bottom of page